አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ  አክስዮን ማህበር አርቲስት ይገረም ደጀኔን እና አርቲስት ትዕግስት ግርማን የብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾመ፡፡

አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ  አክስዮን ማህበር ድርጅቱን ይገልፃሉ ካላቸው  ብራንድ አምባሳደሮች ጋር  ስምምነት ተፈራርሟል።

የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማህበር፣ አርቲስት ትዕግስት ግርማን እና አርቲስት ይገረም ደጀኔን የብራንድ አምባሳደር ማድረጉን አስታውቋል።
የአምባሳደርነት ስምምነቱ በዛሬው  እለት የተደረገ ሲሆን፣ ስምምነቱ ለአንድ አመት የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል።

የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማህበር፣ አርቲስቶቹን የብራንድ አምባሳደር አድርጎ የመረጠበት ምክንያት አርቲስቶቹ በስነ-ምግባር የታነፁ፣በስራዎቻቸውም  በማህበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅ በመሆናቸው ነው ብሏል።

ከኪነጥበብ ስራዎቻቸውም ባሻገር  ሁለቱም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የሚያደርጓቸው መልካምና ለሌሎችም አርአያ መሆን የሚችሉ እንቅስቃሴዎች የብራንድ አምባሳደርነቱን በሚገባ እንዲወጡ እድል ይፈጥርላቸዋል ብሎ እንደሚያምን አክሲዮን ማህበሩ ገልጧል፡፡

ከተመሰረተ አስር ወራትን ያስቆጠረው አክስዮን ማህበሩ፣ የ1 ሺህ 6 መቶ ሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል ማድረጉን የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሮቤል ንጉሴ ተናግረዋል።

የ5 ቢሊየን ብር ካፒታል አክስዮን ከብሔራዊ ባንክ እንደፀደቀለት ያነሱት አቶ ሮቤል አክሲዮኖቹ በሶስት አመት ውስጥ ተሽጦ ያልቃል ብለዋል።
የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አክስዮን ማህበር አገልግሎቱን በጀመረ በ10 ወር ውስጥ ካፒታሉን ወደ 281 ሚሊየን ብር ማድረሱንም አንስተዋል።

በአንድ አመት ውስጥ ቅርንጫፎቹን 50 ለማድረስ እየሰራ የሚገኘው አክስዮን ማህበሩ፣ አሁን ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በባህርዳር፣ደብረብርሃን፣ሃዋሳ ፣አርባምንጭ ፣ድሬዳዋ እና በሃረር ከተማ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ ስራ ማስጀመሩን አስታውቀዋል።

አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የቢዝነስ ክህሎት ሥልጠናዎችን ለመስጠትና የቁጠባና ብድር አገልግሎትን ለማሳደግ አልሞ የተነሳ ተቋም መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፣በተለይም የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የማይችሉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የማህረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ወለድ የብድር አገልግሎት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

“ስኬትን በተግባር” የሚል መሪ ቃል ይዞ የተነሳው አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተከሰተ ያለውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት መቋቋም ያቃታቸውና ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ባላቸው አቅም አማራጭ የስራ መስኮችን እንዲመለከቱ ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ በዝቅተኛ ወለድ መጠን ብድር ማቅረብ፣ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ያልደረሰባቸውን የገጠር ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ፣ “የቆሎ ተማሪ” የተሰኘ የቁጠባና ብድር አገልግሎት መስጠት፣ የፈጠራና ቱሪዝም ስራዎችን በፋይናንስ መደገፍ ላይ በስፋት እስራባቸዋለሁ ሲል መናገሩም አይዘነጋም፡፡

ነሃሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም

Scroll to Top