የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ 3ኛ መደበኛና 3ኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔውን እሁድ ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ ደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ አዳራሽ አካሂዷል፡፡ በዕለቱም የማይክሮ ፋይናንሱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ካሳሁን ደገፉ የተቋሙን የ2023/24 ሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴና የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለአክስዮኖች አቅርበዋል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ በጉባዔው እንደገለጹት በዚህ ፈታኝ ወቅት ተቋሙ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ የሚባል ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉንና የሒሳብ ዓመቱን በስኬት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በሒሳብ ዓመቱ 48 ሚሊዮን ብር ከግብር በፊት ማትረፉን ለባለአክሲዮኑ አቅርበዋል፡፡ ጉባዔውም ከተገኘው ትርፍ ላይ ተቀናሽ የሚደረጉ ወጭዎች ተቀንሰው ለማኅበራዊ አገልግሎት 4% በመመደብ ቀሪውን ትርፍ ለእያንዳንዱ ባለአክሲዮን በሚደርሰው ትርፍ ድልድል መሠረት አክሲዮኑን እንዲያሳድግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ካሳሁን ደገፉ በሰጡት ማሳሰቢያ ሁሉም ባለአክሲዮን ተቋሙን እንዲያጠናክር፣ እንዲደግፍና ያለውን የአክሲዮን ድርሻ እንዲያሳድግ በመጠየቅ ስኬትን በተግባር እንድንኖረው የተቋሙ ባለድርሻዎች ላደረጉት ድጋፍና አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ