አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ በዝቅተኛና በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን የቁጠባ፣ የብድር እና የማይክሮ ኢንሹራንስ አገልግሎት ለማቅረብ በ1,886 ባለአክሲዮኖችና በብር 33,768,000 የተፈረመ መነሻ ካፒታል በመያዝ ዋና መሥሪያ ቤቱን ደብረብርሃን ከተማ በማድረግ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ሥራውን የጀመረ ተቋም ነው።
በአገራችንም ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተጓዳኝ የአነስተኛ ገንዘብ ቁጠባና ብድር እየተስፋፋ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ ከ55 ያልዘለሉ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ተደራሽ የመሆናቸው ዕድል እጅግ ውሱን እንደሆነ እንገነዘባለን። ይህን የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት እና የፋይናንስ ተደራሽነት አለመጣጣም ለመቀነስ አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ስትራቴጂያዊ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ እየሠራ ይገኛል።
ተቋማችን በ7 ክልሎች 53 ቅርንጫፎች በመክፈት 170,000 ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። የተቋማችን ባለአክሲዮኖች ቁጥር 6,104 የደረሰ ሲሆን ተቋማችን ገልግሎቶቹን ለደንበኞቻችን ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል የኮር ባንኪንግ አገልግሎትን ሁሉም ቅርንጫፎች በሲስተም መስራት ጀምረዋል።
ከተመሠረተ ጀምሮ ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለደንበኞቹ ብድር ከ20,000 በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቹ ብድር በመስጠት በተለይም ለግብርና ሥራ፣ ለልዩ ልዩ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ሥራ ማንቀሳቀሻ፣ ለቋሚ ንብረት ማፍሪያ፣ ለቢዝነስ ሥራ ማስፋፊያ፣ ለሴት ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች፣ ከአካል ጉዳት ጋር ለሚኖሩ የማኅበረሰባችን ክፍሎች የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ትኩረት በማድረግ ለአገርና ወገን ዕድገት እየሰራን እንገኛለን።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አንጻር የዲጂታል ባንኪንግ (የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን ቸምሮ ሌሎች በርካታ አማራጮችን የያዘ) መተግበሪያ አልምቶ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅቱን አጠናቋል። በቅርቡም በይፋ ለደንበኞቻችን መገልገያነት የምናውላቸው መሆኑን 3ኛ ዓመት የምሥረታ ዕለታችንን ስናከብር ማብሰራችን ኩራት ይሰማናል።
በመሆኑም የአኩፋዳ 3ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አከባበር ተጀምሯል። በዚህ መርሐ-ግብር ላይ ልዩ ልዩ መሰናዶዎችን በማከናወን የምናከብር ሲሆን፣ ዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም በደብረብርሃን ከተማ የከተማ ማስዋብና ጽዳት በማድረግ በይፋ አስጀምረናል። በቀጣይም በልዩ ልዩ ኹነቶች እያከበርንና ለማኅበረሰባችን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንሰጣለን።
አኩፋዳ ከ460 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በቀጣይም በዋና ዋና የዕድገት ዘርፎች ላይ የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነታችንን እያሳደግን አገር እንገነባለን።
ለመላው የአኩፋዳ ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ በመላው ኢትዮጵያ የምትገኙ ክቡራን ደንበኞቻችን፣ የተዉኣማችን የሥራ መሪዎች፣ ታታሪ ሠራተኞቻችን እና መላው ደጋፊና አጋሮቻችን እንኳን ለ3ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
አቶ አብርሃም ወዳጆ
የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ስኬትን በተግባር!

