እንኳን ለመስቀል በዓል አደረሳችሁ🌼🔥

የሐምሌ ጭፍናውን፣ የነሐሴ ብራውን አልፈን የመስከረም ሰባውን፣ የጥቅምት እሸቱን ይስጠን እየተባለ በወርሐ መስከረም፣ በጸዐዳ ሠማይ፣ በልምላሜ ግምጃ የምድር ገጽ፣ በአበቦች ፍካት፣ በወጣቶች ተስፋ ለሚከበረው ለብርሃነ መስቀሉ እንኳን በሠላም አደረሳችሁ።


የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በስፋት የሚከበር ታሪካዊና ኃይማኖታዊ በዓል ነው። የንግሥት እሌኒ እና የልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ልፋት፣ በርትቶ የመፈለግ፣ የመሻት እና እውነትን የመናፈቅ ንዑድ ምስጢር ነው። የፈለገ የሚያገኝበት፣ የደከመ ፍሬ የሚያይበት፣ የታገሰም ከመዳረሻው የሚዘልቅበት ምሳሌ ነው የመስቀል በዓል።


የመስቀል በዓል በተለየ ቀለምና ድባብ በደቡብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በጉራጌ፣ ጋሞ፣ ሐድያ፣ ከምባታ፣ ሸካ፣ ወላይታ፣ የም፣ ዳውሮ፣ ጎፋ፣ ጌዴዖ እና ሌሎች በርካታ ማኅበረሰቦች ለየት ባሉ ባሕላዊ እና ኃይማኖታዊ ክዋኔዎች በድምቀት እያከበራችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን እንኳን ለዚህ ቀን በሠላም አደረሳችሁ። በሌሎች የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ዘንድም ከዓመት ዓመት በልዩ ክብርና መተሳሰብ የሚከበር አገራዊ በዓል በመሆኑ የመተሳሰብና የበረከት እንዲሆን እመኛለሁ።

ከምንም በላይ የመስቀል በዓል በተለየያዩ አካባቢዎች በሥራ ምክንያት የተነፋፈቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ልጆች ለወላጆች ስጦታዎች ሰጥተው ምርቃት የሚያገኙበት፣ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እና ሌሎች በረከቶችን የሚያገኙበትም ነው።


በዓሉን በማክበር ላይ ያላችሁ የተቋማችን ክቡራን ደንበኞች፣ ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ትጉኃን ሠራተኞቻችን እና አጋሮቻችን እንኳን በሠላምና በጤና አደረሳችሁ። በዓሉን በመተሳሰብና በመረዳዳት እንድናሳልፍ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ።


አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ
የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top