- አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ፣ የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ
የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ ከተቋሙ የሥራ አመራር አባላት እና ከቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች ጋር የ2024/25 ሒሳብ ዓመት የአፈጻጸምን አስመልክቶ የምክክር መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ የተገኙት አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና የዳይሬክተሮች ቦርድ ም/ሰብሳቢ ዲ/ን ካሣሁን ደገፉ ከ45ቱ ቅርንጫፎች ጋር በጋራ የዓመቱን አፈጻጸም ግምገማ በማድረግ በተያዘው የ2025/26 ተቋማዊ ውጤታማነትን እና ትርፋማነትን በማረጋገጥ ለባለአክሲዮኖች እና ማኅበረሰብ እድገት መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ አክለውም አኩፋዳ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ በ7 ክልሎች ከ150 ሺህ በላይ ደንበኞቹን ማገልገል መጀመሩ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ በሂደት ተደራሽነቱን፣ የደንበኞች አያያዝ ሥርዓቱን እና ቅልጥፍናውን በማላቅ ተመራጭ የፋይናንስ ተቋም ለመሆን የጀመረው ጉዞ አመርቂ ነው ብለዋል።
ተቋሙ የፋይናንስ አሰራሩን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ቴክኖሎጅን ከጅምሩ ለመተግበር አስደሳች ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አብርሃም ወዳጆ፣ “የአገልግሎት ቅልጥፍናችን እንዲሻሻልና የደንበኞቻችንን እርካታ ለማሳደግ የቴክኖሎጅ (ኮር ባንኪንግ፣ የሞባይል ባንኪንግ፣ ወዘተ) በተሟላ ደረጃ ለመተግበር የሚያስችሉ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ማይክሮ ፋይናንስ ተቋሙ 45 ቅርንጫፎችን በመክፈት የፋይናንስ አቅርቦት እያደረገ ይገኛል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአጭር ጊዜ 450 ሠራተኞችን በመቅጠር ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በማጠቃለያውም በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት የተሻለ የኦፕሬሽን አፈጻጸም ላስመዘገቡ ቅርንጫፎች ዕውቅና እና ምስጋና ተበርክቶላቸዋል

